Jeremiah 19

1እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ሄደህ፣ ከሸክላ ሠሪ ገንቦ ግዛ፤ ከሕዝቡና ከካህናቱ መካከል ታላላቅ የሆኑትን አንዳንዶቹን ይዘህ፣ 2በገል በር መግቢያ አጠገብ ወዳለው ወደ ሄኖም ልጅ ሸለቆ ውጣ። በዚያም የምነግርህን ቃል ተናገር፤ 3እንዲህም በል፤ ‘የይሁዳ ነገሥታትና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሆይ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ለሰሚው ሁሉ ጆሮ የሚዘገንን ክፉ ነገር እነሆ በዚህ ስፍራ አመጣለሁ፤ 4እኔን ትተውኝ፣ ይህን ስፍራ የባዕድ አማልክት ቦታ አድርገውታልና። እነርሱም ሆኑ አባቶቻቸው፣ የይሁዳ ነገሥታትም ለማያውቋቸው አማልክት ሠውተዋል፤ ይህንም ስፍራ በንጹሓን ደም ሞልተውታል፤ 5እኔም ያላዘዝኋቸውን፣ ያልተናገርኋቸውን፣ ፈጽሞም ያላሰብሁትን፣ ወንዶች ልጆቻቸውን በእሳት ሊሠዉለት ለበኣል መስገጃ ኰረብታዎች ሠርተዋል። 6ስለዚህ ሰዎች ይህን ስፍራ የዕርድ ሸለቆ እንጂ ከእንግዲህ ቶፌት ወይም የሄኖም ልጅ ሸለቆ ብለው የማይጠሩበት ዘመን ይመጣል፤” ይላል እግዚአብሔር

7“ ‘በዚህ ስፍራ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ዕቅድ አፈርሳለሁ፤
አፈርሳለሁ የሚለው የዕብራይስጡ ቃል አነባበብ ገንቦ ከሚለው ጋር ይመሳሰላል (1 እና 10 ይመ)።
በጠላቶቻቸው ፊት ሕይወታቸውን በሚሹት እጅ በሰይፍ እንዲወድቁ አደርጋለሁ፤ ሬሳቸውንም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት ምግብ አድርጌ እሰጣለሁ።
8ይህችን ከተማ ድምጥማጧን አጠፋለሁ፤ ለመሣለቂያም አደርጋታለሁ፤ በዚያም የሚያልፉ ሁሉ ከደረሰባት ጕዳት የተነሣ ወይ ጉድ! ይላሉ፣ ያሾፋሉም። 9የወንዶችና የሴቶች ልጆቻቸውን ሥጋ እንዲበሉ አደርጋለሁ፤ ሕይወታቸውን ለማጥፋት የሚሹ ጠላቶቻቸው ከብበው ሲያስጨንቋቸው፣ አንዱ የሌላውን ሥጋ ይበላል።’

10“ገንቦውንም ከአንተ ጋር በሄዱ ሰዎች ፊት ትሰብራለህ፤ 11እንዲህም ትላቸዋለህ፤ ‘የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የሸክላ ሠሪው ገንቦ እንደ ተሰበረና ሊጠገን እንደማይቻል፣ ይህን ሕዝብና ይህችን ከተማ እንዲሁ እሰብራለሁ፤ የቀብር ቦታ ከመታጣቱ የተነሣ ሙታናቸውን በቶፌት ይቀብራሉ። 12በዚህ ስፍራና በውስጡም በሚኖሩት ላይ ይህን አደርጋለሁ” ይላል እግዚአብሔር። ይህችን ከተማ እንደ ቶፌት አደርጋታለሁ። 13በጣራዎቻቸው ላይ ለሰማይ ሰራዊት ዕጣን የታጠነባቸውና ለባዕዳን አማልክት የመጠጥ ቍርባን የቀረበባቸው፣ የኢየሩሳሌም ቤቶችና የይሁዳ ነገሥታት ቤቶች እንደ ቶፌት የረከሱ ይሆናሉ።’ ”

14ኤርምያስም እግዚአብሔር ትንቢት እንዲናገር ልኮት ከነበረበት ከቶፌት ተመልሶ፣ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አደባባይ በመቆም፣ ለሕዝቡ ሁሉ እንዲህ አለ፤ 15“የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እነሆ ዐንገታቸውን በማደንደን ቃሌን ስላልሰሙ በዚህች ከተማና በዙሪያዋ ባሉ መንደሮች ሁሉ ላይ ላደርስ ያሰብሁትን ጥፋት ሁሉ አመጣለሁ።’ ”

Copyright information for AmhNASV